ዋናዋ ጠላቴ ያመጣኋት ሚስቴ
 ደራሲ - አሚጎ ዞሮመጣ

       ለት ወጣቶች በፖለቲካ ምክንያት ተሰደው ካገር ይወጡና ከብዙ ችግር በኋላ በግራቸው ተጉዘው ሱዳን ይገባሉ፡ ከዚያም እንደማይሆን የለምና ለአራት አመታት ስቃይን በቁና ሲስፍሩ ቆይተው ወንድየው በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮምሽን እርዳታ ካናዳ ሔዶ እንዲኖር ይፈቀድለታል እዚያም ሶስት አመት እንደቆየ ዜግነቱን ያገኝና ሌት ተቀን ስርቶ ገንዘብ አጠራቅሞ ሱዳን ስደተኛ ጣቢያ የምትኖረውን ፍቅረኞውን በሕጋዊ መንገድ ያስመጣትና አንድላይ አንደ ባልና ሚስት ሆነው መኖር ይጀምራሉ ይህ በዚህ እንዳለ በመሃል ሁለት ልጆች ይወለዱና ቀስ በቀስ ፍቅሩ ሲቀዘቅዝ ኑሮው ካቅም በላይ ሲሆን መቸም ያለ ነገር ነውና በሆነ ባልሆነ መጨቃጨቅ መነታረክ ይጀመራል በዚህ ሁኔታ ለጥቂት እመታት አብረው ይቆዩና ወደመጨረሽያ ነገሩ ሲከር ሚስት ባልዋን ሳያስበው ትከሰዋለች ከዚያም ጉዳዩ በጠበቆቻቸው አማካይነት ለሚመለከተው ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ በህጉ መሰረት ዳኛው ፍርዳቸውን ይሰጣሉ - ክዚያ በኋላ ሚስት የምትኖርበት ቤት ሲመረቅላት ባል ግን እጅና እግሩን ይዞ እንዲወጣ ይደረጋል ይህን አስመልክቶ ካገራቸው ውጪ በትዳር የሚኖሩ ሰዎች ለምንና እንዴት እንደማይግባቡ ከሞላ ጎደል ለአንባብያን ትንሽ እውቀት ይሰጣል ብዬ ስለገመትኩ በግጥም መልክ የሚቀጥለውን ድርሰት አቅርቤአለሁ ----


ባል
እኔ ድሮ ሳቅሽ የድሀ ልጅ ነበርሽ
አሁን እዚህ መጥተሽ አጉል ተንቀባረርሽ
ወይ አምላኬ ስትይ የምትበይው አተሽ
 የሱዳን አቧራ አመዳም አድርጎሽ
 ፊትሽ እንኳን ሳይቀር ማዲያት ብቻ ሆነሽ
 ስቃዬን አይቼ እዚህ አመጣሁሽ
 የጥጋብሽ ጥጋብ ውለታዬን ሁሉ ከምንም አልቆጠርሽ

 ሚስት
 አንተ ማን ሆነህ ነው እንዲህ የምትለው
ንሮአችን እንደሆን የሚመሳሰል ነው
አባትህም ቢሆን የጠገበ ሀብታም
ሀብቱን ያካበተው በሀቅ አይመስለኝም
እራስህ ተመልጦ የቅቤ ቅል መስለህ
እንዴት ማድያታም ነሽ ብለህ ትለኛለህ
እንዲህ የምትንቀኝ የምታዋርደኝ
ትንሽ የቀውስ ዘር ያለብህ ምሰለኝ
 
ባል
እንዴት እንዲህ ብለሽ ስሜን ታጠፊያለሽ
የቀውስ ዘር ያለሽ አንቺ ትመስያለሽ
የጠጉርሽ አሰራር የቅንድብሽ መቆም
የምትለብሺው ልብስ ማጠርና መርዘም
የምትናገሪው ቃላት ሁሉ መርዛም
መቀወስሽ እንኩዋን አያጠራጥርም
 
ሚስት
 ለማደርገው ነገር ለምን ተጨነቅህ
አሁን የምኖረው አገር ቤት መሰለህ
ስለኔ አለባበስ የጠጉር አሰራር ምንም አያገባህ
 ከንግዲህ በኋላ የሚበጅ መሰለኝ ብትቀመጥ አርፈህ
 ጭቅጭቅ ካበዛህ እተኛልሀለሁ ከገዛ ጓደኛህ
 
ባል
አሁን ገና ገባኝ ውስጠ ሚስጥርሽ
ከጓደኞቼ አንዱ አንቺን ቢተኛሽ
አትጠራጠሪ ማጅራትሽን ብዬ እንደምገልሽ
ውርደቴን ታቅፌ እንዴት እኖራለሁ
አንችንም ገድዬ እኔም እሞታለሁ
አለያም ካልሆነ ከፎቅ ላይ ዘልዬ እከሰከሳለሁ
 
ሚስት
እንኳን መግደል ቀርቶ ጫፌን አትነካኝም
ከፎቅም ላይ ብትዘል እኔ አያገባኝም
ልጆቹን እንደሆን መንግስት ያሳድጋል
ያንተ እዚህ መጎለት ለኛ ምን ይጠቅማል
 ነገር ሳታበዛ ወደዚያ ብትሄድ ይሻል ይመስለኛል
አሻፈረኝ ብትል ፖሊስ እጠራና አስሮ ያስወጣሀል

ባል
ልጆቼን በትኜ ወዴት እሄዳለሁ
ተቻችሎ መኖር ይሻላል እላለሁ
አለያ ግን ጦሱ ለሁላችንም ነው
ፖሊስ ብትጠሪ ከምንም አልቆጥረው
 
ሚስት
 የማይበርድ ከሆነ ይህ አጉል ትቢትህ
 ፖሊስ ልጠራ ነው እዚህ ቁጭ ብለህ
ከሱ ተነጋገር ከኔ ምንም የለህ

ፖሊስ
በሩን ኩዋ ኩዋ አድርጎ እቤት ይገባና
 ችግሩ ምንድነው እስኪ ወደዚህ ና
አንተነህ ጎረምሳው የምትበጠብጠው
ከሆነስ ሆነና የት ነው የምትሰራው
 መጠጥ ነው ድራግ እንዲህ ያደረገው
 አንድ ሀጢያት ሰርቶ ነው አይኑ የፈጠጠው
 ለምንድነው አንተ የምትረብሸው ?

ባል
እረ እኔ ጌታዬ ምንም አረበሽኩም
 መጠጥም ድራግም ወስጄ አላቅም
ግን አንዳንድ ጊዜ ቢራ እጠጣለሁ
ጠምብዤ ጠጥቼ ማንንም አልነካሁ
 እንዲያው ዝም ብላ ነው እስዋ የጠራችሁ
ስራዬም እንደሆን ዲሽ ወሸር ነበርኩኝ
 ዛሬ ገና ድንገት ሳላቅ ተባረኩኝ

ፖሊስ
እሷ ስራ የላት አንተ ስራ የለህ
 በተለይ አንተማ እንዴት ትኖራለህ
 ያልታወቀ ገቢ አይቀርም ሳይኖርህ
በል አሁን ተነሳ ወደ ጣቢያ እንሂድ
ላጠፋህው ጥፋት ዳኛው እስከሚፈርድ
 አንቺ ደሞ ስሚ የምንነግርሽን
 ቃሉን ተቀብለን ነገ በጠዋቱ እንለቀዋለን
 እስከዚያ ድረስ ግን በደንብ ቆልፊ መስኮት በርሽን
 እገባለሁ ብሎ ችግር ከፈጠረ ቶሎ ብለሽ ጥሪን
 እንደ ፋሲካ በግ እንጎትተዋለን በግር ብረት አስረን
 
ሚስት
አመሰግናለሁ ለትብብራችሁ
 እዚች ከደረሰ እጠራችሁአለሁ
 ልጆች ማሳደጊያ ገንዘብ ስለሌለኝ
 በየወሩ እንዲከፍል ግዳጅ አስገቡልኝ
በሉ በተረፈ በሰላም ዋሉልኝ
 
ዳኛ
ጉዳዩ ምንድነው እስኪ ዘርዝርልኝ
 የተጠራው ፖሊስ ሚስትህን በቡጢ መተሀታል አለኝ
 በል ምንም ሳትዋሽ ሚስጥሩን ንገረኝ
 
ባል
እንኳን መምታት ቀርቶ መጥፎ አልተናገርኳት
 አሁን ምን ያደርጋል ይሄ ሁሉ ውሸት
 እኔ አላቅበትም እንዲህ ያለ ሙግት
 የሚቻል ከሆነ ጠበቃ ይሰጠኝ በተቻለ ፍጥነት
 
ዳኛ
 ጠበቃ መጠየቅ ህጋዊ መብትህ ነው
 ነገር ግን አንተ ነህ ገንዘብ የምትከፍለው

ባል
ከየት አምጥቼ ነው ገንዘብ የምከፍለው
የወር ገቢ የለኝ ወይ ስራ የምሰራው
 ብድር እንኩዋ ሚሰጥ አላቅም አንድም ሰው
መፍትሔ ፈልጉ እንደምንም ብለው
ግራም ነፈሰ ቀኝ ስልጣኑ የርሶ ነው
 
ዳኛ
መንግስት የስጥኅል የግል ጠበቃ
 ሌላ እርዳታ የለም ከዚህ በላይ በቃ
ቀስ በቀስ ከገቢህ እከፍላለሁ ብለህ
 ሕጋዊ ዴኩመንት መፈረም አለብህ

ባል
እሺ እፈርማለሁ ምንም ችግር የለ
መክፈል እችላለሁ ገንዘብ በጄ ካለ
እኔን እንደረዱኝ እግዚአብሔር ይርዳዎ
 አመሰግናለሁ ለትብብርዎ
 
ጠበቃ
 አሁን አነበብኩት የክሱን ሪፖርት
ነገሩ ከባድ ነው እኔ እንዳየሁት
 ጊዜ ያስፈልጋል በጥልቅ ለማጥናት
ሰኞ ወይ ማክሰኞ በሚመጣው ሳምንት
 ስልክ እደውላለሁ ጠብቀኝ በትግስት

ባል
 (ከሳምንት በኋላ )

ምነው ጥፍት አሉ ስልክ ሳይደውሉ
ሳዘጋጅ ከርሜ ማስረጃዬን ሁሉ
 የመጀመሪያው ቀን ሹልክ ብለው ሄዱ በደንብ ሳንተያይ
ታዲያ -- እርሶን ይመስለኛል በየመንገዱ ላይ ቦርሳ የያዘ ሳይ
በነገራችን ላይ እምን አደረሱት ያንን የኔን ጉዳይ

 ጠበቃ
 ምንም ችግር የለ ባንተዋወቅ
ጉዳይህ እንደሆን ይሰራል በሀቅ
 እኔጋ ስላለህ የፍርድቤቱ ፎርም በደንብ የተሞላ
 አያስፈልገንም ማስረጃ መሰብሰብ ከንግዲህ በኍላ
 ትላንት በዚህ ሰአት በቀጠሮ ቀን
 እኔም እረዳቴም እንድላይ ሆነን
ችሎት ቆመን ነበር ምስክር ይዘን
እዳኛው ፊት ቀርበን ስንከራከር
 የሚስትህ ጠበቃ ትንሽ አለው ግር
የኋላ የኋላ ድሉ የኛ እንደሆን አትጠራጠር
 ነገም ይሁን ዛሬ ይዘህልኝ ብቅ በል ሁለት ሺ ብር

 ባል
ስለገንዘብ ጉዳይ ችግር አለብኝ
በየወሩ ልሰጥ ፈርሜአለሁኝ
 የማይሆን ከሆነ እንዳሻሁ ያርጉኝ

ጠበቃ
ያለገንዘብማ ማን ይሰራልሀል
 ነገሩ በንጥልጥል ባለበት ይቆማል
 አንተን አስኮንና ሚስትህ ከረታችህ
 ያልታሰበ ችግር ባንተ ቢደርስብህ
 እኔ ጋ እንዳትመጣ ይረዳኛል ብለህ
 
ባል
የተከራከሩት አንድ ቀን ብቻ ነው
 ሁለት ሽ ብሩ ከየት የመጣ ነው
በሰአት ሀምሳ ብር እንኳ ቢከፈሉ
እንዴት አርባ ሰአት ሰራሁኝ ይላሉ
 ነገሩ ግራ ነው ለሚሰማው ሁሉ
 
ጠበቃ
ብዙ ወጭ አለ አንተ የማታቀው
መዘርዘር አልችልም የግል ጉዳይ ነው
 ላንተ መከራከር ምንም ጥቅም የለው
 ሌላ ጠበቃ አቁም አቤት በል ለዳኛው

 ባል ለዳኛ
 ጌታዬ ነገሩ ተጓተተብኝ
 የሰጡኝ ጠበቃ ገንዘብ አምጣ አለኝ
አስቀድሜ ለርሶ ነግሬዎ ነበር ቤሳ እንደሌለኝ
 የሚቻል ከሆነ ሀቀኛ ጠበቃ ይሰይሙልኝ

ዳኛ

 በትላንትናው ቀን ፍርዱ ተፈርዶብህ ነገሩ እኮ ሞቷል
 እኔ እንደሰማሁት ላንተም ሁኔታውን ጠበቃህ ነግሮሀል
 የፍርዱን ውስኔ አነባለሁ ብትል
ይሕው ግልባጩ ውሰድና አብተልትል

 ፍርድ
ለልጆችህ እናት ግማሹ ከገቢህ ተቆርጦ እንዲሰጣት
 ለፍተህ እንኩዋን ቢሆን የሰራህው ቤቱን ቀንና ሌሊት
 ለሷ ልቀቅላት ልጆችዋን በሰላም ታሳድግበት
 ምክንያት ከሌለህ በምንም ሁኔታ ወደዚያ አካባቢ እንዳትደርሳት
 ልጆችህን ግና በሳምንት አንድ ቀን ይቻላል ማየት
 ሥራ እንደምሰራም ማስረጃ ስላለን በጃችን ኤግዚቢት
ሁለት ሺ ብሩን ለዚያ ለጠበቃህ ክፈለው በፍጥነት
 አለበለዚያ ግን ትዛዝ እሰጣለሁ እንድትገባ እስር ቤት
 የዛሬው ፍርዳችን የመጨረሽያ ነው ይግባኝ የሌለበት
ከንግዲህ በኋላ መልካም ቀን ያርግልህ በል በደህና ሰንብት !

 ==============ተፈጠመ ================


www.ethiocartoons.net.All Rights Reserved.Amigo Zorometa